የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የህብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከዋናው የኃይል ቋት ኤሌክትሪክ ባልደረሰባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች በአማራጭ የኃይል ምንጮች ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለአብነትም በቅርቡ በሶሜል ክልል የተገነባው የቆሪሌ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ተቋሙ በሶሜሌ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች ከዋናው የኃይል ቋት ኤሌክትሪክ የማያገኙ የገጠር ከተሞችና መንደሮች በዲዝል ጣቢያዎች ኃይል እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ነው፡፡
በእነዚህ የዲዝል ጣቢያዎች ከነዳጅ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ከሚሰበስበው ገቢ ጋር የማይመጣጠን የነዳጅ ወጪ በማውጣት ከፍተኛ ለሆነ ኪሳራ እየተዳረገ ነው ተቋሙ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው፡፡
በሶማሌ ክልል በርከት ያሉ በነዳጅ የሚሰሩ የዲዝል ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን፤ ከእዚህም መካከል ዋርደር፣ ቀላፎ፣ ሼኮሽ፣ ሺላቦ እና ሌሎች ከተሞችም ይገኙበታል፡፡
የዲዝል ጣቢያዎቹ በቀን ከ6 እስከ 8 ሰዓት የሚቆይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየሰጡም ነው፡፡
በክልሉ ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የዲዝል ጣቢያዎች በዓመት 740 ሺህ 950 ሊትር ነዳጅና 8 ሺህ 340 ኪ.ግ ዘይት ይጠቀማሉ፡፡ ጣቢያዎቹ በዓመት የሚጠቀሙት ዘይትና ነዳጅ ወደ ገንዘብ ሲቀየር 18,087,241.5 የኢትዮጵያ ብር ነው፡፡
በሌሎች ክልሎች የሚገኙት ቀሪ የዲዝል ሃይል ጣቢያዎች የሚጠቀሙት የዘይትና ነዳጅ ወጪ ሲጨመር ደግሞ ተቋሙ በከፍተኛ ወጪና ኪሳራ ውስጥ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ያሳያል፡፡
በአጠቃላይ ተቋሙ በ2017 ዓ.ም ሁሉም ዜጋ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ከዋናው የኃይል ቋት 65 በመቶ እና ከዋናው የኃይል ቋት በርቀት ላይ ለሚገኙ አካባቢዎች የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በመገንባት በኦፍ ግሪድ 35 ከመቶ ተደራሽ በማድረግ ተቋሙ ለነዳጅና ዘይት የሚያወጣውን ወጪም ሙሉ በሙሉ ያስቀራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
የሶማሌ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት 45 ሺህ 119 ደንበኞች፣ 3 ሺህ 999 ኪሜ የመካከለኛና 1 ሺህ 400 ኪ.ሜ የዝቅተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም 988 የዲስትርቢውሽን ትራንስፎርመሮች አሉት፡፡
ምንጭ: የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
You are not authorised to post comments.
Comments will undergo moderation before they get published.