Ethiopian Energy^Power Business Portal,eepBp

ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል የታሪፍ ጭማሪ በአራት ዓመታት ውስጥ በአማካይ እስከ 345 በመቶ እንደሚያድግ ቢገለጽም፣ በኪሳራ ሲቀርብ የቆየውን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደማይደጉም መንግሥት አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ከምክትል ሥራ አስፈጻሚው አቶ ደመቀ ሮባ ጋር በመሆን ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ ላለፉት 12 ዓመታት ሲሠራበት የቆየው ታሪፍ በኪሎ ዋት በሰዓት 1.8 የአሜሪካ ሳንቲም ሲከፈልበት የቆየ መሆኑን፣ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ከሰባት እስከ ስምንት የአሜሪካ ሳንቲም ጭማሪ የሚደረግበት የታሪፍ ማስተካከያ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ጭማሪው የ345 በመቶ አማካይ ዕድገት እንዳለው ያሳያል፡፡

ከሦስት ሚሊዮን በላይ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች በዚህ ታሪፍ እየተስተናገዱ ነው፡፡ የኢንዱስትሪና የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎችም ከዚህ የተለየ ታሪፍ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ይደረግላቸው የነበረው ድጎማ ሙሉ በሙሉ መነሳቱም ታውቋል፡፡

እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች አኳያ አዲሱ ታሪፍ በግማሽ ያህል ያንሳል ያሉት አቶ ሽፈራው፣ የተደረገው ማስተካከያ በኪራሳ የቆየው ተቋም የኦፕሬሽን ሥራዎች እንዳይቆሙ ለማገዝ ይረዳዋል እንጂ ወጪዎቹን ሙሉ ለሙሉ አይሸፍንለትም ብለዋል፡፡ የተጣለው ታሪፍ ከ50 ኪሎ ዋት ጀምሮ እስከ 200 ኪሎ ዋት ለሚጠቀሙ ደንበኞች ድጎማ ማደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ እስከ 50 ኪሎ ዋት በወር ለሚጠቀሙ ምንም ዓይነት የታሪፍ ለውጥ አልተደረገም ብለዋል፡፡ ከ50 እስከ 100 ኪሎ ዋት ለሚጠቀሙ እስከ 75 በመቶ ድጎማ ሲደረግ፣ እስከ 200 ኪሎ ዋት ለሚጠቀሙም የ25 በመቶ ድጎማ ተደርጓል፡፡

የታሪፉ ሥሪት የመክፈል አቅምን መሠረት ያደርጋል ያሉት አቶ ሽፈራው፣ ደንበኞች የኃይል አጠቃቀማቸው ላይ ቁጠባ እንዲለምዱ የሚያስገድድ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ ይህም ይባል እንጂ የወጣው ታሪፍ በየደረጃው ሲታይ ጭማሪው እስከ 700 በመቶ ጭማሪ የታየባቸው የታሪፍ ይዘቶች እንዳሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ለአብነት ያህል በወር 400 ኪሎ ዋት ኃይል የሚጠቀሙ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች፣ በታኅሳስ ወር በወጣው የዚህ ዓመት ታሪፍ መሠረት በኪሎ ዋት በሰዓት የሚከፍሉት 0.9750 ብር ነው፡፡ ይህም በወር ሲሰላ 390 ብር ይሆናል፡፡ በመጪው ዓመት ለተመሳሳይ ፍጆታ የሚጣለው ታሪፍ ወደ 1.3833 ብር በኪሎ ዋት በሰዓት ይጨምራል፡፡ ይህም ማለት ወደ 553 ብር ያድጋል ማለት ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም. ለ400 ኪሎ ዋት የሚከፈለው በሰዓት ፍጆታ 1.7917 ብር በመደረጉ፣ በጠቅላላው ከ716 ብር በላይ መክፈል ይጠበቃል፡፡ በአራተኛው ዓመት መጨረሻ ማለትም ታሪፉ ሙሉ ለሙሉ በሚተገበርበት ዓመት የ400 ኪሎ ዋት ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች 880 ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ታሪፉ በዚህ ደረጃ በዝቶብናል ያሉ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያውም እንደ ታሪፉ ሁሉ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ መንግሥት ሊያጤነው ይገባል ይላሉ፡፡ ይኸውም ታሪፉ በማይጨመርበት የ50 ኪሎ ዋት ኃይል ላይ ለድኅረ አገልግሎት አሥር ብር ቢጣልም፣ ከ50 ኪሎ ዋት በላይ በሚጠቀሙ ላይ ግን 42 ብር ተጥሏል፡፡ ይህም ማለት 60 ኪሎ ዋት የተጠቀመ ደንበኛ 42 ብር ለአገልግሎት ይከፍላል ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር 100 ኪሎ ዋት ኃይል መጠቀም የሚያስችለውን ክፍያ በአገልግሎት ስም መክፈል አግባብ አይደለም የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡

እንዲህ ያለው የታሪፍ ጭማሪ ተጠቃሚውን በሁለት መንገድ ተጎጂ ያደርገዋል፣ መንግሥት በኃይል ፍጆታ ላይ ያደረገው ጭማሪ የዋጋ ንረት ያስከትላል የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ በተጠቃሚው ላይ ብቻም ሳይሆን በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ታሪፉ ተጥሏል፡፡ ይህም አምራቾቹ ጭማሪውን መልሰው ወደ ሸማቹ ስለሚያሻግሩ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች በሁለት መንገድ የታሪፉ ተጎጂ መሆናቸው እንዴት ነው የታየው ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አቶ ሽፈራው መሟገቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ተቋሙ በኪሳራ ወደ ሥራ ማቆም እያዘገመ ባለበት ወቅት ቢያንስ የኦፕሬሽን ሥራዎቹን ለማስኬድ የተደረገ ማስተካከያ ነው ያሉት አቶ ሽፈራው፣ በአሁኑ ወቅት የሠራተኛ ደመወዝን ጨምሮ ከውጭ የሚገቡም ከአገር ውስጥ የሚገኙም ቁሳቁሶችና ግብዓቶች ዋጋ ከ12 ዓመታት በፊት ከነበረው ዋጋ አኳያ ያሳዩት ለውጥ በአዲሱ ታሪፍ ሙሉ ለሙሉ አይሸፈንም፡፡ በዚያም ላይ በርካታ ፕሮጀክቶች በብድር እየተገነቡ በመሆናቸው፣ ዕዳውን ለመክፈል ጭምር የታሪፍ ለውጥ ማድረጉ ተገቢ እንደሆነ ሞግተዋል፡፡ በመሆኑም የተደረገው ለውጥ ከሸማቹ አቅም በላይ እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡

ከታሪፉ ባሻገር የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ጥራት፣ በየጊዜው የሚያጋጥመው መቆራረጥና ብልሽት ባለበት ወቅት ጭማሪው ተገቢ አይደለም የሚልም ስሞታ ይመጣል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባን ጨምሮ በስምንት ዋና ዋና ከተሞች የኔትወርክ ማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ፣ በአሁኑ ወቅትም 94 በመቶ የተገባደደው ሥራ በዓመቱ መጨረሻ እንደሚጠቃለል አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚታየውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን የሚቀንስ አቅርቦት ለመዘርጋት ከቻይና መንግሥት በተገኘ 162 ሚሊዮን ዶላር የሚካሄደው የማሻሻያ ፕሮጀክት፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ አፈጻጸሙ 75 በመቶ መድረሱን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በድኅረና በቅድመ ክፍያ የሚስተናገዱ ደንበኞች፣ ክፍያ ለመፈጸም በርካታ እንግልት እየገጠማቸው ሲማረሩ ቆይተዋል፡፡ በቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች የሚገለገሉ ደንበኞች በዓመቱ መጨረሻ በሞባይል፣ በኢንተርኔት፣ በኪዮስኮችና በሱፐርማርኬቶች በኩል ክፍያ የሚፈጽሙበት የዲጂታል ሥርዓት እንደሚተገበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚው አቶ ደመቀ ገልጸው፣ የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞችም ከነሐሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ክፍያቸውን የሚፈጽሙበት አሠራር እንደሚዘረጋ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በድኅረ ክፍያ የሚጠቀሙ ደንበኞች በክፍያ ለሁሉ በኩል የሚስተናገዱበት አሠራር እንደሚቋረጥም ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

በካርድ የሚሠሩት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች በአብዛኛው ብልሽት እንደሚገጥማቸውና ለማደስ በሚቀርበው ጥያቄ የተቋሙ ባለሙያዎች ስለቆጣሪዎቹ ያላቸው ዕውቀት የተወሰነ በመሆኑ፣ ችግር ሲያጋጥም መቆየቱን የሚገልጹ የተቋሙ የክፍያ ጣቢያ ኃላፊዎች አሉ፡፡ ባለሙያዎቹ የቆጣሪዎቹን ችግሮች ቢበዛ 50 በመቶ ብቻ ቢያውቁ ነው የሚሉ አስተያየቶች ቢሰነዘሩም፣ አቶ ደመቀ የተጋነነ ብለውታል፡፡

የግብፅ ኤል ስዌዲ ግሩፕ ኩባንያ እህት በሆነው ኤሌክትሮሜትርስ አክሲዮን ማኅበርና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽርክና የሚተዳደረው ፋብሪካ በአገር ውስጥ የሚያመርታቸው ቆጣሪዎች በአብዛኛው ችግር አለባቸው የሚለውን የማይቀበሉት አቶ ደመቀ ምናልባት በሰዎች ንክኪ፣ ሆን ብለው በማበላሸትና በኤሌክትሪክ የቴክኒክ ችግሮች ምክንያት በሚከሰቱ ብልሽቶች ከቆጣሪዎቹ ውስጥ እስከ አሥር በመቶ የሚገመቱት ለብልሽት ሊዳረጉ ይችላሉ ብለው ያምናሉ፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች ለደንበኞች መሠራጨታቸውን የገለጹት አቶ ደመቀ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደረገ ማጣራት ከአሥር ሺሕ በላይ ደንበኞች ለአንድ ዓመት ያህል ለተጠቀሙበት ኃይል ክፍያ እንዳልፈጸሙ ተደርሶባቸዋል፡፡ ይህም የሆነው ቆጣሪዎቹ እንደ ድኅረ ክፍያዎቹ ወርኃዊ ንባብ የማይካሄድባቸው በመሆኑ ምክንያት ይህንን ተገን አድርገው፣ ቆጣሪዎቹን በመክፈት ንባባቸውን በካርድ ላይ እንዳያሳዩ በማድረግ የማጭበርበር ድርጊቶች መታየታቸውን አክለዋል፡፡ በመሆኑም በቋሚነት የፍተሻ ሥራዎች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ስድስት ወራት ካከናወናቸው የኃይል አቅርቦት ሥራዎች ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡ ከኢነርጂ ሽያጭ 3.23 ቢሊዮን ብር ሲሰበስብ፣ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ከነበሩ ውዝፍ ሒሳቦች ከ665 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡ ዕቅዱ 872 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ሒሳብ ለመሰብሰብ እንደነበርም አስታውቋል፡

Source: ethiopianreporter

0
0
0
s2smodern

Comments powered by CComment

eepBp tweeter Feed

eepBp Facebook feed

Join eepBp Community